2 ዮሐ 1

Study

   

1-2 በእኛ ስለሚኖርና ከእኛ ጋር ለዘላለም ስለሚሆን እውነት፥ እኔ ሽማግሌው በእውነት ለምወዳቸውና እኔ ብቻ ሳልሆን እውነትን የሚያውቁ ሁሉ ደግሞ ለሚወዱአቸው ለተመረጠች እመቤትና ለልጆችዋ፤

3 ከእግዚአብሔር አብና ከአብ ልጅ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም በእውነትና በፍቅር ከእኛ ጋር ይሆናሉ።

4 ትእዛዝን ከአብ እንደ ተቀበልን ከልጆችሽ በእውነት የሚሄዱ አንዳንዶችን ስለ አገኘኋቸው እጅግ ደስ ብሎኛል

5 አሁንም፥ እመቤት ሆይ፥ እርስ በርሳችን እንድንዋደድ እለምንሻለሁ፤ ይህች ከመጀመሪያ በእኛ ዘንድ የነበረች ትእዛዝ ናት እንጂ አዲስ ትእዛዝን እንደምጽፍልሽ አይደለም።

6 እንደ ትእዛዛቱም እንሄድ ዘንድ ይህ ፍቅር ነው፤ ከመጀመሪያ እንደ ሰማችሁ፥ በእርስዋ ትሄዱ ዘንድ ትእዛዙ ይህች ናት።

7 ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ገብተዋል እነርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የማያምኑ ቸው፤ ይህ አሳቹ የክርስቶስ ተቃዋሚው ነው።

8 ሙሉ ደመወዝን እንድትቀበሉ እንጂ የሠራችሁትን እንዳታጠፉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።

9 ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት።

10 ማንም ወደ እንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤

11 ሰላም የሚለው ሰው በክፉ ሥራው ይካፈላልና።

12 እንድጽፍላችሁ የምፈልገው ብዙ ነገር ሳለኝ በወረቀት በቀለም ልጽፈው አልወድም፥ ዳሩ ግን ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ወደ እንተ ልመጣ አፍ ለአፍም ልገራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ።

13 የተመረጠችው የእኅትሽ ልጆች ሰላምታ ያቀርቡልሻል።